የ130 ኣመት የእንቦጭ ማስዎገድ ልምድና ለጣና የሚሰጠው ትምህርት
============================
ዕንቦጭ ለአሜሪካዋ ሃገረ ግዛት ፍሎሪዳ የትናንት ክስተት ኣይደለም – ይልቁንም ከ1884 እ.ኤ.አ ጀምሮ እስከ አሁን የዘለቀ ከዕንቦጭ ጋር እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ እንጂ። በፍሎሪዳ ግዛት ለሚገኘው የኦኮቾቤ ሃይቅ ደግሞ ከ1980ዎቹ ጀምሮ ፈተና ሆኖበት እስካሁን ዘልቋል። የመቆጣጠር ስራዉም ቢሆን አንዴ በዘመቻ ያለቀ ሳይሆን ትዉልድ ተፈራርቆበታል። ብዙ ምርምርና ጥናት ተካሂዶበታል። የተለያዩ የመከላከል ዘዴዎች ተሞክረው ጠቃሚዎቹ ኣሁንም ድረስ እየተሰራባቸው ይገኛል። እናም ችግሩ በቅርብ ለደረሰብን ለእኛ ይህንን ልምድ መዉሰድ የጣናን ዕንቦጭ ለማስዎገድ በእጅጉ አስፈላጊ በመሆኑ የባለሙያዎችን ቡድን ወደ ስፍራው ልከን የልምድ ልውውጥ አድርገን ነበር።
የጣና ችግር ኣዲስ ከመሆኑ ጋር ታያይዞ ያለውን የዕውቀት ክፍተት ለመሙላት የተቋቋመው የዓለማቀፉ ጣናን መልሶ የማቋቋም ማህበር የምርምር ቡድን ከአማራ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጋር በመሆን የፍሎሪዳዉን ልምድ ሰሞኑን ቀስመዋል። ባለሞያዎቹ ስለችግሩ ከመመራመር በተጨማሪ በኣካል ተገኝተው የመከላከል ስራዉን በኣካል ኣይተዋል። ከፍሎሪዳ ግዛት ከፍተኛ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች ጋርም መክረዋል፤ ልምድ ተለዋውጠዋል። ይህም ጣና ላይ ለሚደረገው ጥረት ጥሩ ግብአት ይሆናል።
ጉብኝቱን ያደረጉት ተመራማሪዎች የተረዱት የመጀመሪያው ነገር ቢኖር ዕንቦጭን የማስዎገድ ስራ የአንድ ወቅት የዘመቻ ስራ ሳይሆን ተከታታይ ዘርፈ-ብዙ ስራን የሚጠይቅ መሆኑን ነው። ስራው ለኣንድ ወገን የሚተው ሳይሆን የተቀናጀ የመንግስት ቁርጠኝነትና የህዝብን ተሳትፎ፤ እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ርብርብ የሚጠይቅ ነው።
የፍሎሪዳ ተሞክሮ አንደሚያሳየው እንቦጭን ለማስዎገድ መጀመሪያ የተጠቀሙት እኛ አሁን እያደረግነው እንዳለነው በማሽነሪ ነበር። እየዋለ እያደር ግን ሌሎችንም አማራጮች መጠቀም ግድ ብሏቸዋል። በተለይም ባዮሎጅካልና ኬሚካል ጭምር መጠቀም ስርጭቱን መግታት አስችሏቸዋል።
ምንም አይነት አካባቢያዊና ስነ-ህይወታዊ ተጽእኖ የሌላቸው (EPA approved) ኬሚካሎች በፍሎሪዳ ጥቅም ላይ እንዳዋሉት ለመረዳት ችለዋል። ነገር ግን ኬሚካል ጣና ላይ ከመጠቀም በፊት በሃይቁ ላይ ላሉ ዕፅዋትና አሳዎች መጥፎ ጉዳት እንዳያስከተል ምርምር ከወዲሁ መጀመር አንዳለበት ተገንዝበዋል። ኬሚካል ከመጠቀም በፊትም የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማዳበር ስራም ከወዲሁ ሊሰበት እንደሚገባ ተስማምተዋል። ዘላቂ ምርምርና ክትትልም የፌደራልና የክልል ምስሪያ ቤቶችን ድጋፍ ያሻዋል ተብሏል።
በጉብኝቱ ተሳታፊ የነበሩት የክልሉ ኣካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ሃላፊ ዶ/ር በላይነህ አየለ እንዳሉት ከማሽን ግዢው ጎንለጎን የማህበሩ ባለሙያዎች የምርምርና ጥናት ስራ በመስራትና ስልጠና በመስጠት ለሃገር ዉስጥ ባለሞያዎች የእዉቀት ሽግግር የሚያደርጉት አስተዋጾ ሊበረታታ የሚገባው አብይ ስራ መሆኑን አስረድተዋል። የማህበሩ ምክትል ሰብሳቢና የምርምር ቡድን አባል የሆኑት ዶ/ር ማርታ ዳኘው ከካናዳ በራሳቸው ወጭ ይህንን ትምህርታዊ ልምድ ለመቅሰም መምጣታቸውን አድንቀው፤ በፍሎሪዳ Department of Water Management ሲኒየር ሃይድሮሎጂስትና የማህበሩ የቦርድ አባል የሆኑት ዶ/ር ይርጋለም አሰግድ የልምድ ልውውጡን በማመቻቸታቸው አመስግነዋል።
Melkamsew Kebede
GCLTR Public Relation Officer