መልካም ዜና
የእንቦጭ ማጨጃ ማሽኑ ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ ተልኳል::
ጣናን የወረረውን እንቦጭ አረም ለማስወገድ እንዲረዳ 27 ሜ ኪዩብ ባንዴ ማጨድ የሚችል ሁለት ትላልቅ ማጨጃ ማሽኖች እያንዳንዳቸው ከነሙሉ መለዋወጫቸው $172, 970 የአሜሪካን ዶላር በመክፍል በአጠቃላይ $342,940 ዶላር ወጭ በማድረግ ማዘዛችን የሚታወስ ነው:: በቅርቡም ከፋብሪካው መረከባችንን አሳውቀን ነበር::
የመጀመሪያው ማሽን ዛሬ በመርከብ ወደ ኢትዮጵያ ተልኳል:: በኮረና ቫይረስ ስርጭት ምክንያት የወደብ ስራው በመታወኩ March ላይ መላክ ከነበረበት ጊዜ መዘግየት ቢከሰትም ከኢትዮጲያ መርከቦች ድርጅት ጋር በጋራ በወሰድናቸው አድካሚ የመፍትሄ አማራጮች ተሳክቶ ዛሬ ተልኳል::
በተለይ ማሽኑ የተመረተበት ሃገር ካናዳ በቫይረሱ ስርጭት ምክንያት የቶሮንቶ ወደብ እንቅስቃሴን በመግታቷ ማሽኑ ወደብ ላይ ቁጭ ብሎ ከሚጠብቅ ሌሎች የወደብ አማራጮችን መፈለግ ነበረብን:: የኢትዮጵያ መርከቦች ድርጅት በአሜሪካ ካሉ ወደቦች ወደ ጂቡቲ ዕቃ የሚያጓጓዝ መርከብ በማፈላለግና ወጭውን በመሸፈን ትልቅ ድጋፍ አድርጎልናል:: ከዛም የቅርብ ቀን የጉዞ የጊዜ ሰሌዳ ያለው መርከብ ከባልቲሞር ወደብ በማግኘት እንዲጫን ተባብሮናል:: እኛም ማጨጃ ማሽኑን ከካናዳ ወደ ባልቲሞር ወደብ (Baltimore, MD) በማጓጓዝ ማሽኑ ቶሎ መርከብ ላይ ተጭኖ ወደ ኢትዮጵያ እንዲላክ አድርገናል::
ይህ ሁሉ ጭንቀታችን ማሽኑ ከክረምቱ ወቅት ቀድሞ ጣና ላይ ቢደርስ የዝናቡን ወቅት ተከትሎ የሚታየውን የእንቦጭ መስፋፋት በመግታት በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል በማለት ነው::
ማሽኑ ሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ ኢትዮጵያ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል::
ይህ እንዲሆን ገንዘባቸውን ያዋጡ በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን የሃገር ሃብት የሆነውን ጣናን ለማዳን የሰራችሁትን አኩሪ የትብብር ስራ ታሪክ ሲያስታውሳችሁ ይኖራል:: በዋሽንግተን ዲሲ: በሜሪላንድ: ቨርጂኒያ: ዳላስ: ቺካጎና በእንግሊዝ ለንደን የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን: የሃይማኖት ተቋማት: አንጋፋ አርቲስቶችና ሙዚቀኞች ስለመልካም ስራችሁ ከፍ ያለ ምስጋናችን ይድረሳችሁ! የማህበሩ አባላትም ጉልበታችሁን: እውቀታችሁን: ገንዘባችሁንና ጊዜያችሁን በነጻ በመስጠት ለሰራችሁት ስራ ምስጋና ይገባችኋል:: ስንተባበር እንዲህ ያማረ ስራ መስራት እንችላለን!
ሁለተኛውን ማሽን ለመላክ ደሞ እንቅስቃሴያችንን በቅርቡ እንጀምራለን::
ጤና ለጣና ይስጥልን!
ዓለማቀፉ ጣናን መልሶ ማቋቋም