From: BBC Amharic

የጣና ሐይቅ በእምቦጭ አረም መወረሩን ተከትሎ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አረሙን በእጅ በመንቀል ለማስወገድ ሲረባረቡ ቢስተዋልም ባለሞያዎች የዚህ መሰሉን እንቅስቃሴ ውጤታማነት እንዲሁም በማሽን የመንቀልን ዘመቻ ተግባራዊነት ይጠራጠራሉ፤ ሐይቁ ላይ የተጋረጠው አደጋ ግን ይህ ብቻ አይደለም።

ከአገሪቱ ጨው አልባ የተፈጥሮ ውሃ ውስጥ ሃምሳ በመቶ ያህሉን የያዘው የጣና ሐይቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በእምቦጭ አረም መወረሩ የተስተዋለው እ.አ.አ በ2011 ነው።

አራት ሺህ ሄክታር ያህል የውሃ ክልልን በመሸፈን የጀመረው የአረሙ ወረራ፤ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 20ሺህ ሄክታርን ወደማካለል አድጓል።

በወቅቱ የክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ጽህፈት ቤት እምቦጭን “ጣናን የወረረው እጅግ አስከፊው አረም” ሲል የፈረጀው ሲሆን፤ በሐይቁ ዙርያ የሚኖሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባብር አረሙን በእጅ በመንቀል ለማስወገድ ተጥሯል።

በዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት እንዲሁም ከመንግሥታዊ ቢሮዎች ጋር በትብብር የተሰናዳው “የጣና ሐይቅ የእምቦጭ አረም መከላከያ ቁጥጥር ስትራቴጅ” እ.ኤ.አ ከጥቅምት 2011 አንስቶ እስከ ታህሳስ 2013 ድረስ እምቦጭን በእጅ መንቀል ላይ የፈሰሰው ጉልበት በትንሹ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ይገመታል።

ይሁን እንጅ በጥቂት ዓመታት ጊዜ ውስጥ አረሙ መጠኑን ከእጥፍ በላይ ጨምሮ በመመለስ ሐይቁን ወሯል።

በአሁኑ ሰዓት 50ሺህ ሄክታር የሐይቁ ክፍል በአረሙ እንደተወረረ የሚገመት ሲሆን፤ ይህም ከአዲስ አበባ ጠቅላላ የቆዳ ስፋት በአራት ሺህ ሄክታር ብቻ የሚያንስ ነው።

128 ኪሎሜትር ያህል የሐይቁ ዳርቻ በእምቦጭ መሸፈኑም ይገመታል።

በአረሙ እና በሐይቁ ላይ ምርምሮችን ያደረጉት በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የሥነ-ሕይወት ባለሞያው ዶክተር ሰለሞን ክብረት ለእምቦጭ ዳግም ምፅዓት አንደኛው ምክንያት አረሙን በእጅ ነቅሎ ለማጥፋት በተሞከረበት ወቅት ንቃዩን በአግባቡ ለማስወገድ ትኩረት ባለመሰጠቱ ነው ይላሉ።

“የተነቀለው አረም በሙሉ ለሐይቁ ዳርቻ ቅርብ የሆነ ቦታ ላይ ተትቶ ስለነበር፤ ብዙም ሳይቆይ በዝናብ አማካይነት ከዚያ ቀደም ደርሶባቸው ወደማያውቅባቸው ሰፊ ቦታዎች ሁሉ ሊወሰድ በቅቷል” ሲሉ ዶክተር ሰለሞን ለቢቢሲ ያስረዳሉ።

“መጥፎው ዜና [እምቦጭን] ሙሉ በሙሉ ማጥፋት እምብዛም የማይቻል መሆኑ ነው” ይላሉ ዶክተር ሰለሞን አክለው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ “ዘሩ እስከሰላሳ ዓመት ድረስ መቆየት የሚችል መሆኑ ነው።”

መጤው አጥፊ

እምቦጭ መነሻውን ላቲን አሜሪካ ያደረገ፤ እንዳሻው በውሃ ላይ የሚንሳፈፍና የሚዋልል ወራሪ አረም ሲሆን በተለያዩ መንገዶች ወደአፍሪካና እስያ እንደተሰራጨ ይነገራል።

ይህ ተክል የተለያዩ ጉዳቶችን የሚያስከትል ሲሆን፤ ጉዳቶቹን የሚያደርስበት መንገድም የውሃ ፍሰትን በመከልከል፣ ውሃው ውስጥ ያሉ ተክሎች እና እንስሳት የፀሐይ ብርሃን እንዳይደርሳቸው በመከልከል፣ አሳን የመሰሉ እንስሳት ኦክስጅን እንዳያገኙ በማፈን ጭምር ነው።

ከዚህም በዘለለ በእርከን ሥራ፣ በኃይል ማመንጨት እንዲሁም በዓሳ ማጥመድ ላይ ተፅዕኖ አለው።

የእምቦጭ አረም ከጠቅላላ አካሉ ውስጥ 90 በመቶ ያህሉ ውሃ እንደመሆኑ ብዙ ውሃን ይመጣል።

እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ አጋማሽ የአዋሽ ወንዝን በመገደብ በተሰራው የቆቃ ሐይቅ ላይ ለመታየቱ ማስረጃዎች አሉ። በተለያዩ ጊዜያት የጫሞና የአባያ ሐይቆችን ጨምሮ በሌሎች የአገሪቱ የውሃ አካላት ላይ የእምቦጭ ወረራ ተስተውሏል።

“የጣና ሐይቅ የእምቦጭ አረም መከላከያ ቁጥጥር ስትራቴጂ” ሐይቁ እንዴት በዚህ መጤ አረም ሊወረር እንደቻለ በትክክል ማወቅ እንዳልተቻለ ይገልፅና ከውጭ ሀገራት የገቡ ያገለገሉ የዓሳ ማጥመጃ መሳሪያዎች፣ ጀልባዎች አሊያም በእርሻ ግብዓቶች አማካይነት ሊሆን እንደሚችል ግምቶች መኖራቸውን ይጠቅሳል።

አረሙ ጣናን ከመውረሩ አስቀድሞ ሱዳን ውስጥ መታየቱንም “ስትራቴጅው” ያስታውሳል።


የጣና አስፈላጊነት

ጣና ለዓለም ሥነ-ምኅዳራዊ ብዝሃነት ያስፈልጋሉ ከተባሉ 250 ሐይቆች መካከል አንዱ ሆኖ ተመርጧል። በውስጡ 28 የዓሳ ዝርያዎችን የያዘ ሲሆን ከእነዚህ መካከልም 21 ያህሉ በሌላ ቦታ አይገኙም።

በዙሪያው የሚኖሩ ከ3 -4 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሐይቁ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አላቸው። ከእነዚህም መካከል ሐይቁ በያዛቸው 37 ደሴቶች የሚገኙ ከ15ሺህ በላይ የኅብረተሰብ አካላት ይገኙባችዋል።

ከጣና ሐይቅ የሚገኝ ዓመታዊ የዓሳ ምርት የገንዘብ ተመን 1.1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሆነ የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ያሳውቃል።

ጣና በየዓመቱ 13ሺህ ቶን የሚደርስ ዓሳ የማምረት አቅም ቢኖረውም፤ ከ1000 ቶን የሚበልጥ ዓሳ ሲያመርት አይስተዋልም።

የእምቦጭ ወረራ የሐይቁን ብዝሃ ህይወት አደጋ ላይ የጣለ መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ።

ተመራማሪው ዶክተር ሰለሞን እንደሚሉት ከሆነ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የሐይቁ የዓሳ መጠን በ75 በመቶ ያህል እንደቀነሱ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

የሐይቁን ሰሜናዊ ዳርቻ ታከው የሚገኙ ሩዝ አምራቾች እስከ 500 ሄክታር የሚደርስ መሬትን በአረሙ ምክንያት አጥተዋል ይለዋል።

“የአረሙ ተፅዕኖዎች በአካባቢው ኗሪዎች ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ ጀምረዋል። ተገቢ የቁጥጥር እርምጃዎች በአፋጣኝ ተግባራዊ የማይሆኑ ከሆነ ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ህልውና አደጋ ይጋረጥበታል” ሲሉ ዶክተር ሰለሞን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ተገቢ እርምጃዎች”

ዶክተር ሰለሞን ከአማራ ክልል ባለስልጣናት እና ከዩኒቨርስቲ አካላት ጋር ባደረግኩት ውይይት አረሙን በማሽን ለማጥፋት የመሞከር አማራጭ ከፍ ያለ ተቀባይነት እንዳለው ተገንዝቤያለሁ ይላሉ።

ማሽኖችን መጠቀም አረሙን በፍጥነት ለማስወገድ የሚያስችል አማራጭ አንደመሆኑ የብዙሃንን ድጋፍ ሲያገኝ ይስተዋላል።

የክልሉ የአካባቢ፣ ደን እና የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ የባህርዳር እና ጎንደር ዩኒቨርስቲዎችን በማስተባበር የተሻለ ውጤት ያላቸው አማራጮችን ለመጠቀም፤ እንዲሁም አረሙን ከነቀለ በኋላ ፈጭቶ ወደባዮጋዝ ምንጭነት የሚቀይር ማሽንንም ሥራ ለማስጀመር እየተጣረ መሆኑን በቅርቡ ገልፀዋል።

እ.ኤ.አ ከ2014 እስከ 2018 ላሉት ዓመታት የተቀረፀው “የጣና ሐይቅ የእምቦጭ አረም መከላከያ ቁጥጥር ስትራቴጂ” በበኩሉ የተቀናጁ እርምጃዎችን መውሰድን ይመክራል።

በቅንጅት ቢተገበሩ ይበጃሉ ከተባሉት እርምጃዎች መካከልም የእጅ ነቀላ፣ የማሽን ነቀላ እና ሥነ-ህይወታዊ የቁጥጥር መንገድ ይገኙባቸዋል።

ዶክተር ሰለሞን የማሽንን አማራጭ ከአገሪቱ የገንዘብ አቅም አንፃር አዋጭ አይደለም ይሉታል።

“ማሽኖቹን ለማንቀሳቀስ ከሚያስፈልገው ገንዘብ በተጨማሪ ማሽኖቹ የሚንቀሳቀሱባቸው ወደቦች እንዲሁም የሚታጨደውን አረም የማጓጓዣ መንገዶች አስፈላጊ ናቸው። እነዚህ ደግሞ አሁን የሉም” ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ችግሩ በነካቸው አስራ ስምንት ቀበሌዎች መንገዶችን፣ ወደቦችን እንዲሁም የማራገፊያ ስፍራዎችን መስራት ግድ ሊሆን ነው ይላሉ ዶክተር ሰለሞን ጨመረው።

ተመራማሪው ይህንን ሙግታቸውን ባተቱበት ጽሁፋቸው እንደሚሉት ደግሞ፤ አንድ አረም የመንቀያ ማሽን በቀን ውስጥ ማካለል የሚችለው ስፍራ ከአስር ሄክታር አይበልጥም።

በመሆኑም 10 ማሽኖች ጣናን የወረረውን እምቦጭ አረም የማስወገድ ዘመቻ ላይ ቢሳተፉ እንኳ አረሙን አስወግዶ ለመጨረስ አምስት መቶ ቀናት ወይንም ከአንድ ዓመት ተኩል የሚልቅ ጊዜ ያስፈልጋል።

ከሌሎች አረሙን የማስወገጃ መንገዶች መካከል ኬሚካሎችን መርጨት አንዱ ሲሆን ይህ መንገድ ግን ሐይቁ ለያዛቸው እንስሳትና ተክሎች አደገኛ መሆኑ አያጠያይቅም።

ለዶክተር ሰለሞን ሥነ-ሕይወታዊ የቁጥጥር መንገድ ካሉት አማራጮች ሁሉ ከወጭ አንፃር አዋጭ የሆነው እንዲሁም በውጤታማነቱ የተሻለው ነው።

ይህ መንገድ ሥነ-አካባቢያዊ ጉዳት በማያደርስ ዘዴ ተፈጥሯዊ ጠላቶችን መጠቀምን የሚከተል መንገድ ሲሆን ሁለት የጢንዚዛ ዝርያዎች አረሙን በማስወገድና ስርጭቱንም በመቆጣጠር ውጤታማ ሆነው ተገኝተዋል።

ስለዚህም ከሰላሳ በላይ አገራት ይህንን ስልት ተግባራዊ በማድረግ ውጤት አስመዝግበዋል።

የሌሎች ገራት ተሞክሮዎች

እምቦጭ የበርካታ ሀገራት የውሃ አካላት ላይ አደጋን የሚጋርጥ ሲሆን ለምሳሌ ያህል ጎረቤት ሱዳን ለእምቦጭ ቁጥጥር በየዓመቱ 1 ሚሊዮን ፓውንድ እንደምታወጣ ይዘገባል።

ኡጋንዳ በበኩሏ የቪክቶሪያ ሐይቅን የወረረውን አረም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር የቻለች ሲሆን ከተከተለቻቸው መንገዶች ውስጥ ሥነ-ሕይወታዊ የቁጥጥር መንገድ አንዱ ነው።

ይህን የቁጥጥር ስልት ሙሉ በሙሉ በተግባር ላይ አውሎ ውጤትን ለማግኘት ዘለግ ያለ ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑ ግን አረሙን በአፋጣኝ ከማስወገድ ግብ ጋር የሚቃረን ነው።

ዶክተር ሰለሞን ግን ሁለቱን የጢንዚዛ ዝርያዎች በኢትዮጵያ እንዲራቡ እና ይህንን ሥራ እንዲያከናውኑ ማድረግ እንደሚቻል የምርምር ውጤቶች እንደሚጠቁሙና በዓመት አራት ጊዜ እንዲራቡ ማድረግ እንደሚቻል ይገልጻሉ።

ሌሎች ፈተናዎች

የአካባቢው ወንዞች አፈርና ዝቃጭ የሚይዙ መሆናቸው አረሙ በጣና ሐይቅ እንዲፋፋና እንዲስፋፋ አግዟል። የሐይቁን የሥነ-ሕይወት ኅልውና የሚፈታተነው አደጋ ግን እምቦጭ ብቻ አይደለም።

በሐይቁ ዙርያ ያሉ ፋብሪካዎች የሚለቁት የውሃ ፍሳሽ ለውሃው ጥራት መጓደል ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል።

በሐይቁ ዙርያ ያለው የሕዝብ ብዛት እየጨመረ መሄድ የሐይቁን ተፈጥሯዊ ሃብት እያመናመነው እንደሆነ የሚያስረዱ ጥናቶችም አሉ።

በጣና ሐይቅ ላይ የዓሳ ማጥመድ እንቅስቃሴ 400ሺህ ያህል የሚሆኑ የማኅበረሰብ አካላት የህልውና ምንጭ ነው።ከእነዚህ አካላት መካከል ከሐይቁ ዓሳ በማጥመድ የሚተዳደረው ቢተው ካሰኝ ይገኝበታል።

ቢተው የዓሳው ቁጥር መመናመን የውሃው በእምቦጭ ከመሸፈን ጋር ተደማምሮ ለኅልውናው ስጋት እንዲገባው እንዳደረገው ይናገራል።

“ወትሮ በአንድ ሳምንት የምናገኘው አሁን ወር ያለፋናል” ይላል።

በጣና ሐይቅ የዓሳ ሃብት መመናመን ዙርያ እሸት ደጀን እና አጋሮቻቸው ያደረጉት ጥናት እንደሚያመላክተው ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሐይቁ የሚጥመድ ዓሳ መጠን ክፉኛ አሽቆልቁሏል።

እ.ኤ.አ በ1993 በአንድ ጉዞ 177 ኪሎ ዓሳ ይጠምድ የነበረ ሲሆን ይህ ቁጥር ግን በ2010 ወደ56 ኪሎ አሽቆልቁሏል።

ከዚህም በተጨማሪ የጣና ሐይቅ ኃብት አስተዳደር ምርምር ማዕከል ሐይቁ የአፈር መሸርሸር፣ የአካባቢ ብክለት፣ የአሸዋ ቁፋሮ፣ የሐይቁን ዳርቻ ታክከው ያሉ በተለይም ሩዝ አምራች ገበሬዎች ደካማ የመሬት አጠቃቀም ልማዶች እና የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን ተጋፍጧል ይላል።

በእነዚህ ሁሉ ፈተናዎች የተከበበው ጣና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አትኩሮትን የሚሻበት ደረጃ ላይ ደርሷል።