የእንቦጭ ማጨጃ ማሽን ለአማራ ክልል መንግስት በስጦታ ተሰጠ።
PRESS RELEASE (Washington DC, United States)
ተቀማጭነቱ በአሜሪካ የሆነው ዓለማቀፉ ጣናን መልሶ ማቋቋም ማህበር በሰሜን በአሜሪካና በእንግሊዝ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር እንዲሁም ከደብረገነት የኢ/ኦ/ተ/ ቤተክርስቲያን (ዋሽንግተን ዲሲ) ባገኘው ድጋፍ በ5.8 ሚሊዮን ብር የገዛውን የእንቦጭ ማጨጃ ማሽን ዛሬ ባሀር ዳር ደርሶ ለክልሉ መንግስት በስጦታ ተሰጥቷል። ይህ ማሽን በአንዴ 28 ሜትር ኪዩብ አረም በአንዴ ማረምና መሸከም የሚችል ሲሆን 75 የፈረስ ጉልበትም አለው። ማህበሩ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ድጋፎች ሲያደርግ መቆየቱ ያታወቃል በተለይም በ2010 ዓ.ም. የእንቦጭ ማጨጃ ማሽን በስጦታ መስጠቱ ይታወሳል። ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ የስልጠናና የቴክኒክ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። ማህበሩ ባለፈው ዓመት ከክልሉ አካባቢ ጥበቃ ቢሮና ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ባለሙያዎችን ዩጋንዳ ወስዶ በእንቦጭ አወጋገድ ስልቶች ዙርያ ስልጠናና ልምድ እንዲቀስሙ ማድረጉ ይታወሳል።
ዓለማቀፉ ጣናን መልሶ ማቋቋም ማህበር በውጭ ሃገር በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን የተመሰረተ የበጎ አድራጎት ማህበር ነው። የማህበሩ አባላትም በነጻ ለሃገራቸው ድጋፍ ለማድረግ የተሰባሰቡ በአካባቢ ጥበቃና ውሃ አያያዝ ዙርያ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው በጎ ፍቃደኞችን ያካተተ ነው።
ማህበሩ ጣናን ከተደቀነበት አደጋ ለማዳን በሚሰራው ስራ ውስጥ የሚያበረክተውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የማህበሩ ዋና ሰብሳቢ ዶ/ር ሰለሞን ክብረት አስታውቀዋል። ማህበሩ ሌላ የእንቦጭ ማጨጃ ማሽን በካናዳ አሰርቶ የጨረሰ ሲሆን
ሰሞኑንም ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልከው የማህበሩ ሰብሳቢ ዶ/ር ሰለሞን ገልጸዋል። የክልሉ መንግስት የሚረከባቸውን የእንቦጭ ማጨጃ ማሽኖች በአግባቡ ተጠቅሞ የእንቦጭን ሽፋንን ለመቀነስ ቁርጠኛ ስራ መስራት ይጠበቅበታል።
እሸቴ ምስጋናው
የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር
Global Coalition for Lake Tana Restoration