ወቅታዊ መረጃ ስለመስጠት
አለም ዓቀፍ የጣና መልሶ ማቋቋም ማህበር ጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ከተቋቋምበት ጊዜ አንስቶ የተቀናጀ ተግባር ስናከናውን መቆየታችን ይታወሳል፡፡
ቀደም ሲል ከለገስነው የአረም ማስወገጃ ማሽን በተጨማሪ በተለያዩ የአሜሪካና የአውሮፓ ከተሞች ባሰባሰብነው ገንዘብ ሁለት H-9 905 የተሰኙ አረም ማጨጃ ማሽኖች እያንዳንዳቸው 75 የፈረስ ጉልበት ያላቸውና በአንድ ጊዜ 26.2 ሜትሪክ ኪዩብ አረም ማጨድ የሚችሉ ሁለት ማሽኖች ከነሙሉ መለዋወጫቸው ከካናዳው አኳማሪን ኩባንያ ማዘዛችን ይታወሳል::
የማሽኑ ግዥ ከፈፀምንበት ውል አንፃር በዚህ ወር ማስረከብ ቢጠብቅባቸውም የተወሰነ መዘግየት በመፈጠሩ ይህንን ለእናንተ ማሳወቅ እንሻለን::
በትናንትናው ዕለት የማህበራችን ማኔጅመንት ባልደረባ ካናዳ ኦክቪል ከተማ በፋብሪካው በመገኘት ማሽኖቹ ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ ተመልክቷል:: ከኩባንያው ጋር ተወያይተዋል::
በጉብኝቱም:-
1) ማሽኖቹ ውጫዊ አካል ተገንብቶ ማለቁን:
2) አንደኛው የማሽኑ ተንሳፋፊ አካል ቀለም ተቀብቶ ማለቁንና የአረም መሰብሰቢያ ኮንቬየር ቀበቶዎችም ተሰርተው መጠናቀቃቸውን:
3) የውሃ ፍሳሽ ሙከራ እየተደረገ መሆኑን: ሌሎች የሃይድሮሊክ ሲስተሞች ለመገጣጠም ዝግጁ መሆናቸውን:
4) መዘግየት የተፈጠረው ኩባንያው የመርከቦችን ሞተር ከሚያቀርብለት ኩባንያ ሞተሮቹ ዘግይቶ በመረከቡ መሆኑን ከይቅርታ ጋር ገልፆልናል::
5) የማሽኖቹ ሞተሮች የተገዙት ከታዋቂው የአሜሪካው ጆን ዲር በመሆኑ ትዕዛዝ ላይ ጊዜ መውሰዱን ገልፀው::
6) ማሽኖቹን በቀጣይ ከአራት እስከ አምስት ሳምንታት ውስጥ ባለው ጊዜያት ተጠናቀው እንደሚያስረክቡን ገልፀውልናል::
የጉብኝቱ ፎቶዎች ተካተዋል::
በጉብኝቱም ወቅት ፍሪያማ ውይይት ከማድረግ ባሻገር በተከታታይ ወደ ፋብሪካው እየሄድን ያለውን ለውጥ እንደምንከታተል ተግባብተናል:: የሚቀጥለው የጉብኝት ጊዜ ሜይ ወር መጀመርያ ላይ ይሆናል::
ማሽኖቹን ለመግዛት በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር በዲሲ፤ ዳላስ፤ ቺካጎ፣ ለንደንእንዲሁም በዲሲ የደብረገነት መድሃኒያለም የሚገኙ የጣና ሀይቅ ወዳጆችና መላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የማሽን ግዥው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅና ለጣና ሀይቅ መልሶ ማቋቋም ዘላቂ ሥራዎች ስላደረጋችሁልን ቀና ትብብርና ስላሳያችሁን ትግስት በማህበሩ ሥም ላቅ ያለ ምስጋናችን እናቀርባለን::