ዓለም አቀፍ ፍ የጣና መልሶ ማቋቋም ማህበር ወቅታቂ መረጃ

 August 2018 

ዓለም አቀፍ የጣና መልሶ ማቋቋም ማህበር በጣና ሀይቅ የተከሰተውን የእንቦጭ ወራሪ አረም ለማስወገድ፣የሀይቁን ጤንነት ለመመለስና አንዲሁም የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት በዘላቂነት ለመጠበቅ የተመሰረተ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ ማህበሩ በግል ተነሳሽነት በባለሙያዎች የተቋቋመና በዳይሬክተሮች ቦርድ የሚተዳደር ነው፡፡

ማህበሩ ቀን .. ኦገስት 2 ቀን 2018 . የዳይሬክተሮች ስብሰባ አካሂዷል፡፡ በስብሰባው የተለያዩ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት ተካሂዷል፡፡ የቀጣይ በጀት ዓመት ሥራዎችም ከስትራቴጅክ ዕቅዱ ጋር በተስማማ መልኩ ተዘጋጅቷል፡፡ በማህበሩ ሕገደንብ መሰረት የዳይሬክተሮች ስብሰባ ውሳኔዎች ለአባላትና ለባለድርሻ አካላት ማሳወቅ አንዱና ዋነኛው ተጠያቂነት መርህ በመሆኑ የስብሰባውን መረጃዎች በተመለከተ በዚህ አጭር መግለጫ አንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

የዓመቱ ዕቅድ ክንውን

ማህበሩ ባሳለፍነው በጀት ዓመት በዕቅድ ከያዛቸው ተግባራት መካከል፡የእንቦጭ ማጨጃ ማሽን በማቅረብ የአረሙን  ስርጭት መቀነስ፣ ለየክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠትና የሳይንሳዊ የቁጥጥርና ክትትል አሰራሮችን መዘርጋት ይገኙበታል።

በዚህ መሰረት የተከናወኑ ተግባራት ቀጥለው ቀርበዋል፡፡

  • ሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ ባለ 25 የፈረስ ጉልበት የእንቦጭ ማጨጃ ማሽን ተገዝቶ ጣና ላይ ስራ መጀመሩ ይታወቃል። የሳይንቲፊክ ኮሚቴው ባቀረበው ጥናት መሰረት ሁለት ተጨማሪ ከፍተኛ ጉልበት ያላቸው ማሽኖች መጨመሩ የአረሙን መከላከል ስራ እንደሚያፋጥነው ተጠቁመዋል፡፡ አሁን ጣና ላይ እየሰሩ ያሉት ሁለት ማሽኖች (አንዱ በማህበሩ የተገዛ ነው) አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፡፡ በማህበሩ የተገዛው ማሽን መካከለኛና ዝቅተኛ አረም ስርጭት ባለባቸው አካባቢዎች የበለጠ ውጤታማ ነው፡፡ የእንቦጩ ስርጭት ጥቅጥቅ ያለበት ቦታ ላይ አሁን ካለው ማሽን የበለጠ የፈረስ ጉልበት ያለው (100 የፈረስ ጉልበት በላይ) እንደሚያስፈልግ በመስክ ጥናት ተለይቷል። በዚህም መሰረት ከፍተኛ የፈረስ ጉልበት ያለው ማሽን ለመግዛት ከተለያዩ አምራች ድርጅቶች የማሽኖችን ስፔስፊኬሽን እየሰበሰብን ነው።   
  • በአቅም ግንባታ ዘርፍ የማህበሩ አባላት የራሳቸውን ወጪ በመሸፈን ለስድሰት ጊዜያት ወደ ጣና በመሄድ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ ለሁለት ጊዜያት የዘመናዊ የመረጃ ሥርዓትን በመጠቀም ነባራዊ የአንቦጭ አረም ሥርጭትን፣ ስፋትና መጠን በተመለከተ መረጃዎች አሰባስቧል፡፡ ይህንን መረጃ መሰረት በማድረግ አጠቃላይ አንቦጭ የሚወገድብትን ስልት ተነድፏል፡፡ በመሆኑም የአንቦጭን አረም ለማስወገድ ምን ዓይነት የማሽን ዓይነት፣ ምን ያህል መጠን፣ የሰው ሀይልና የባሎጅካል መቆጣጠሪያ አንደሚያስፈልግ በጥናት ተለይቷል፡፡ በዚህ በተቀናጀ አሰራር በአጭር ጊዜ ውስጥ ከግማሽ በላይ አረሙን ሥርጭት መቀነስ ተችሏል፡፡
  • አምስት የሳይንቲፊክ ኮሚቴ አባላት በተለያየ ጊዜ በራሳቸው ወጪ ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ የተለያዩ ስልጠናዎችም ሰጥተዋል፡፡የክልሉን አካባቢ ጥበቃ ቢሮን በዕውቀታቸው ደግፈዋል፤ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቱ ምሁራን ጋር ስትራቴጂክ ዶክመንት በማዘጋጀት ስራ አግዘዋል። የእንቦጩን ስርጭት ክትትልና ቁጥጥር (monitoring and evaluation system) አሰራር ለመዘርጋት ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር መክረዋል። ስልጠናም ሰጥተዋል።
  • ከማሽኑ ጎን ለጎን የባዮኮንትሮል በሚቀጥለው ዓመት ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ይህ ዘዴ ለአረም መከላከል የሚሆኑ የነፍሳት አይነትን ማራባትና በሀይቁ ላይ ማሰማራትን ያካትታል፡፡ ይህንን ዘዴ ከጎንዮሽ ጉዳት ነጻ በሆነ መልኩ ለማከናወን በቂ ስልጠናና ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ባለፉት በርካታ ወራት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች በግሪን ሃውስ ዉስጥ በሰፊው ተጠንቶ አሉታዊ ጎን እንደሌለውና አዋጭ ዘዴ መሆኑ ተረጋግጧል። ማህበራችን ይንን ስራ በመደገፍ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያለው የሳይቲፊክ ቡድናችን ባለሙያ  ወደ ተግባር የሚገባበትን አሰራር ለመዘርጋት ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፤ ከክልሉ አካባቢ ጥበቃና ከግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት የተውጣጡ የባዮኮንትሮል ቡድን አቋቋሞ እየሰራ ነው። በቅርቡም ይህ ቡድን ወደ ዩጋንዳ በመጓዝ ከዩጋንዳ ባለሙያዎች ጋር የልምድ ልውውጥና የመስክ ጉብኝት በማድረግ ስራውን ጣና ላይ ለመስራት የሚያስችል የትግበራ ማኑዋል (implementation guideline) ያዘጋጅና ወደ ስራ ይገባል።

ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ያለን ትብብር

  • በዋናነት በጣና ሐይቅ ዙሪያ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለማጥፋትና በዘላቂነት ጤናማ ስነምህዳር አንዲኖረው ለማስቻል በጣና ሀይቅ ላይ ከሚሰሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፤ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፤ ከሴክተር መስራቤቶችና ከክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ ጋር በመተባበር የተለያዩ ድጋፎችን ስናደርግ ቆይተናል፡፡ በዶ/ ማማሩ ሞገስ (ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ) አስተባባሪነት ከተለያዩ /ቤቶች የተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን ጋር በጋራ በመሆን የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ ዶክመንት ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ የዚህ ሰነድ ዝግጅት ለቢሮው በቀጣይ  ጣና ፈንድን  ለመጠቀምና እንዲሁም ከሌሎች የመንግስት አከላት ድጋፍ ለማግኘት ይረዳል፡፡ በበጀት ዓመቱ የሚከናወኑ ተግባራትን በግልጽ ስለሚያስቀምጥ ለአፈጻጸም ያግዛል፡፡                     
  • ከፌደራል የአካባቢ ጥበቃ ሚነስቴር መስሪያ ቤት ጋር በመተባበር በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ስራ ለመስራት የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ሃላፊ በፍሎሪዳ የሚሰራውን የረጅም አመታት የእንቦጭ ማስወገድ ስራ ቦታው ድረስ ሄደው ዕውቀት እንዲገበዩ በማድረግና ከከፍተኛ ባለሙያዎች ልምድ እንዲቀስሙ በማድረግ ማህበራችን አበይት ስራ አከናውኗል። ይህም የተለያዩ የእንቦጭ ማስወገድ ስልቶች መሬት ላይ ሲተገበር በማየት ተጨባጭ ዕውቀት ለመቅሰም አጋጣሚዉን አመቻችተናል። ይህም አመራሩ መሬት ላይ በተግባር በቀሰሙት ዕውቀት ለጣና የሚያስፈልጉ የእንቦጭ አወጋገድ ስልቶች እንዲዘረጉ እረድቷል።
  • ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲና የጣና ተፋሰስ የተቀናጀ በጎ አድራጎት ማህበር  ጋር በመተባበር በጣና ሀይቅ ላይ የሚደረጉ ጥናቶች እንዲሁም በመረጃ የተደገፈ ክትትልና ቁጥጥር ስራ ላይ የቴክኒክ ድጋፎች እየተደረጉ ይገኛል፡፡

ዓመታዊ ፋይናንስ ሪፖርት

  • በአጠቃላይ በአመቱ ውስጥ ማህበሩ ባካሄዳቸው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች (አትላንታ፤እስራኤል፤ዲሲ፤ ቺካጎ፤ ኒውዚላንድ)፣ በኦንላይን ገቢማሰባሰቢያና ፣ በተለያዩ መንገድ ከተገኙ ገቢዎች በድምሩ 269,142 የአሜሪካ ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፣በያዝነው ዓመት ለመጀመሪያው ማሽን ግዥና ለሁለተኛው ማሽን ግዥ ቅድመ ክፍያ፣ ለጥናት፣ አንዲሁም ሌሎች ወጭዎችን ጨምሮ በድምሩ $124,447 ወጪ ተደጓዋል፡፡ ከወጪ ቀሪ በአካውንታችን $145,695 የአሜሪካ ዶላር ይገኛል፡፡

ያለ ምንም ልዩነት ለጣና ጤንነት!

እሸቴ ምስጋናው

የአለም ዓቀፍ የጣና ሀይቅ መልሶ ማቋቋም ማህበር

የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር