Date: 12 October 2018
ወቅታዊ መረጃ
ዓለማቀፉ ጣናን መልሶ ማቋቋም ማህበር ወደ ስራ ከገባበት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብዙ ስራዎችን ከውኗል። ማህበሩ አራት የድጋፍ ስራዎች ላይ በዋናነት ይሰራል –
 1. የአረሙን ባህርያትና ስርጭት ለማወቅ የሚረዱ የተለያዩ ጥናቶችን ማድረግ፤
 2. የአረም ማስወገድ ስራን የሚያግዙ መሳሪያዎች ድጋፍ ማድረግ፤
 3.  የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መስጠትና
 4.  የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን (monitoring and evaluation) ማጠናከር ናቸው።

እነዚህን ስራዎች ለመከወን የሚያስፈልገውንም ገንዘብ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር የገቢ ማሰባሰቢያ ስራዎች ተካሂደዋል። በማህበራችን ድረ-ገጽ ላይ (www.tanacoalition.org) የሚሰሩ ስራዎችንና የየሶስት ወር የፋይናንስ ሪፖርቶችን ለህዝብ በግልጽ እያቀረብን እንገኛለን። በአመቱ ውስጥ በዋናነት የሰራናቸው ስራዎችም፤

 1. የእንቦጩን ባህሪ፤ ቁጥጥርና አወጋገድ ላይ ግንዛቤ ለማሳደግ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ከተቋቋመው የጣና ተፋሰስ የተቀናጀ ልማት በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር የተለያዩ ጥናቶች ተሰርተዋል። ባለሙያዎችን በተለያየ ጊዜ ወደ አካባቢው በመላክም ጣና ላይ ለሚሰራው ስራ ድጋፍ እና ክትትል አድርገናል።
 2. ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የአምስት አመት ጣናን ከእንቦጭ የመቆጣጠርና ተፋሰሱን መልሶ የማቋቋም ስትራቴጂክ ዶክመንት ዝግጅት ላይ ሙያዊ ድጋፍ ሰጥተናል፤
 3. የመስክና የሳተላይት መረጃዎችን በማጠናከር የእንቦጭ ስርጭት ካርታ በማዘጋጀት፤ በመረጃ የተደገፈ ስራ እንዲካሄድ አስተዋጾ አድርገናል።
 4. እንቦጭ ጣና ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በተመለከተ ሃገር-አቀፍና ዓለም አቀፍ ግንዛቤ እንዲፈጠር የድርሻችንን አበርክተናል።
 5. አንድ ማሽን ገዝተን አስረክበናል። በቀጣይም ሁለት የተለያዩ ማሽኖችን (harvester and airboat) ለመግዛት እንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን።
 6. ከፌደራል አካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጋር በመተባበር ስራው በዕውቀት ላይ የተመረኮዘ እንዲሆን የክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ ከፍተኛ ባለሙያ ፍሎሪዳ በመሄድ በኦቾቤ ሃይቅ ላይ ያለውን የእንቦጭ አወጋገድ ልምድ እንዲቀስሙ እና ፤ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር እንዲመካከሩና ትምህርት እንዲወስዱ ድጋፍ አድረገናል።
 7. የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ እያካሄደ ያለውን እንቦጭን በስነ ህይወታዊ ዘዴ የመቆጣጠር ስራን ከሙከራ ወደተግባር እንዲገባ ድጋፍ እያደረግን ሲሆን በቅርቡም ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲና ከክልሉ አካባቢ ጥበቃ የተውጣጡ ባለሙያዎች የሚስተፉበት በስነ ህይወታዊ ዘዴ እምቦጭን ማስወገድ ዙሪያ ስልጠና በዩጋንዳ እንዲይካሄድ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን። ይህም ስልጠና ስራውን ከሙከራ ወደ ተግባር የሚያሸጋግር የትግበራ ሰነድ (implementation guideline) ለማዘጋጀት ይረዳል ብለን እናምናለን፤
 8. የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም (UNEP) በቅርብ ባከሄደው ጣናን ከእንቦጭ ለመታደግ የሚመክር ስብሰባ ላይ በመገኘት የጥናት ውጤቶቻችንን ያቀረብን ሲሆን ለወደፊቱም ሊሰሩ የሚገቡ ተግባራትን ነቅሰን በማውጣት ሃሳባችንን አጋርተናል፡፡ UNEP ሊያዘጋጀው ባሰበው ፕሮፖዛል ላይም የድርሻችንን ለማበርከት ተመዝግበናል።

የማሽን ግዥ በተመለከተ

በማሽን የታገዘ እንቦጭን የማስወገድ ስራን ለመደገፍ ማህበራችን ከዚህ ቀደም ገዝቶ ከአስረከበው ማሽን በተጨማሪ ሌሎች ከፍተኛ ጉልበት ያላቸው ማሽኖችን ለመግዛት በእንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን።ነገር ግን የሚቅጥሉትን ማሽኖች ለመግዛት ሊመለሱ የሚገባቸው ጥያቄዎች አሉ። ለምሳሌ አሁን የምንገዛቸው ማሽኖች ከባለፈው ምን ምን ማሻሻል የሚገባው ነገሮች አሉ? ከዚህ በፊት የላክነው ማሽን ኦፐሬሽኑ ምን ይመስላል? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ በቀጣይ የሚገዙ ማሽኖችን ምን ዓይነት መሆን አለባቸው ለሚለውን ተገቢ መልስ ያሰጣል። እነዚህ ጥያቄዎችን ለመመለስ ደግሞ ጊዜ ወስዶ የባለሙያ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል። ለዚህም ነው ማሽኖችን ለመግዛት እስካሁን ጊዜ የወሰድነው። የአረም ማጨጃ ማሽኖች ላይ ልምድ ያለው ገምጋሚ ባለሙያ ሃገር ውስጥ አለመኖሩ ጥናቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ለማቅረብ አስቸጋሪ አድረጎታል። ከብዙ ልፋት በኋላ ግን እነዚህን ማሽኖች ላይ ከፍተኛ ልምድ ያለው ባለሙያ ከናይጀርያ አግኝተናል። ባለሙያው ወደ ኢትዮጵያ ሄዶ የማሽኑን ኦፐሬሽን እንዲገመግምና ተጨማሪ የኦፐሬሽን ስልጠናዎች እንዲሰጥ በማሰብ ባለሙያው በቅርብ ቀን ወደ ኢትዮጵያ ይላካል። ባለሙያው የማሽኑን አሰራር ከገመገመልን በኋላ የግምገማ ውጤቱን እንደ ግብአት በመጠቀም የሚቀጥለውን ማሽን ግዥ እንጨርሳለን። ይህም በከፍተኛ ዋጋ በህዝብ ገንዘብ የሚገዙ ማሽኖችን ጥራት እና የአገልግሎት ብቃት ለማረጋገጥ የታለመ ነው።

ከዚህ በፊት የተገዛው ማሽን በመካከለኛና አነስተኛ የአረም ሽፋን ላለበት ቦታ ተስማሚ ሲሆን በቀጣይ የሚገዙ ማሽኖች ደግሞ ከፍተኛ የአረም ሽፋን ላለባቸው ቦታዎች የሚስማማ ይሆናል። ለዚህም ሲባል የማህበራችን ሳይንቲፊክ ቡድን በተለያዩ ሃገራት የሚመረቱ የአረም ማጨጃ ማሽኖችን ስፔስፊኬሽን አወዳድሯል። ለማወዳደርም የተጠቀምንበት የመመዘኛ መስፈርቶች የሚከተሉት ነበሩ፤

 • ከፍተኛ የፈረስ ጉልበት ኖሮት በአንዴ ከ20ሜ ኪዩብ በላይ መሰብሰብ የሚችል፤
 • ከዚህ በፊት በተለያዩ ሃገሮች (በተለይ በአፍሪካ መልከአምድር) ተሞክሮ ጥሩ ውጤት ያሳየ፤
 • የመለዋዋጫ ዕቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ የሚችል (ለምሳሌ ከአማጋው ማሽን የተማርነው አንዱ ተግዳሮት በቂ የመለዋወጫ ጥሬ እቃዎችን ማቅረብ ባለመቻሉ የማሽኑ ጥገና ብዙ ጊዜ መውሰዱ ነበር)፤
 • ማሽኑን ለማሰራት ከፍተኛ ሙያ የማይጠይቅ፤
 • የጥገና ዋጋው ተመጣጣኝ የሆነና በሃገር ውስጥ ባለሙያ ሊጠገን የሚችል፤
 • የማሰሪያ ወጭው ውድ ያልሆነ፤
 •  ቢያንስ የ2 ዓመት ዋስትና ያለው፤
 • የማሽኑን አጠቃቀም ስልጠና መስጠት የሚችል፤
 • ለማጓጓዝ አመች የሆነ (ቢቻል የተገጣጠመ) እና፤
 • የማሽኑ የግዥ ዋጋ ተመጣጣኝ የሆነ ናቸው። እነዚህን መመዘኛዎች ያሟሉ ሁለት ማሽኖችን ተለይተዋል።

አንደኛው ዊስኮንሲን የሚገኘው አኳሪየስ ሲስተመስ የሚያመርተው Series 800 የተባለው ማሽን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አኳማሪን የሚያመርተው H9-905 የተባለው ማሽን ነው። ሁለቱም ከ75 የፈረስ ጉልበት በላይ ያላቸው ሲሆን የዊስኮንሰኑ 23.5ሜ ኪዩብ (ወይም 7,076 ኪሎግራም) የመሸከም አቅም ሲኖረው የአኳማሪን ማሽን ደግሞ 26.6ሜ ኪዩብ (ወይም 9,070 ኪግ) ነው። ዋጋቸው ደግሞ የዊስኮሰኑ USD 222,170 ሲሆን የአኳማሪኑ USD150,000 ነው። ሁለቱንም ማሽኖች በተለያዩ አፍሪካ ሃገራት ላይ በስራ ላይ ያሉ ሲሆን ከሁለቱም የማሽን አምራቾች ጋር የማህበራችን የሳይንስ ቡድን ሰፋ ያለ ውይይትና ጥናት አድርጓል። የአኳማሪኑ ማሽን ዋጋው ተመጣጣኝ የሆነው አምራቹ በየዓመቱ ብዙ ማሽኖችን ስለሚሸጥ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችለናል። በዚህ ሰአት የምንጠብቀው የናይጀሪያው ባለሙያ ጣና ላይ ያለውን ማሽንና አሰራር አይቶ የሚሰጠውን የሶስተኛ ወገን ሙያዊ ትንታኔ ብቻ ነው።

ከላይ እንደተጠቀሰው የማህበራችን ዓላማ በጣና ላይ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ድጋፍ መስጠት ነው። የስራው ባለቤትና ማሽኑን ቀንተቀን ተከታትሎ በጀትና የሰውሃይል መድቦ የማንቀሳቀስ ሃላፊነት ያለበት የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ሲሆን የእኛ ድርሻ ጥናት አድርጎ ማሽኖችን ገዝቶ ማስረከብ ነው። ስለዚህ የክልሉ አካባቢ ባለስልጣን ቢሮ ማሽኖችን ተቆጣጥሮ የማሰራት ሃላፊነት አለበት። በተደጋጋሚ እንደገለጽነው እና በስታራቴጂክ ዶክመንቱ ላይም እንደሰፈረው ጣናን የሚያስተዳድር ራሱን የቻለ ተቋም ቢቋቋም ጣናን ከእንቦጭ ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋምና ለመንከባከብ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን። የክልሉ የአካባቢ ጥበቃ፤ ደንና ዱር አራዊት ባለስልጣን ሌሎች ተደራራቢ ስራዎች (ለምሳሌ የደን ጥበቃና አስተዳደር እንዲሁም የዱር አራዊት ጥበቃን እና ሌሎችም) ያሉት ስለሆነ ጣናን በዘላቂነት የመንከባከብ ስራ ወጥና ራሱን በቻለ መልኩ በዘላቂነት ተቋማዊ አወቃቀር ኖሮት ጣናን የሚያስተዳድር ተቋም ሊቋቋም ይገባል። ለዚህም የፌደራልና የክልሉ መንግስት ወጥነት ያለው በቂ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል። ይህም ጣና ላይ የሚሰራውን ስራ ዘላቂነት ያለው ተቋማዊ ቅርጽ አስይዞ ለማስቀጠል ይረዳል። ተቋሙም እስከ ቀበሌ የሚወርድ መዋቅር በመዘርጋት ማሽኖችን የሚከታተል፤ ስነ ህይወታዊ ስራን የሚያስፈጽም፤ ህብረተሰቡን የሚያስተባብር፤ እንዲሁም ክትትልና ቁጥጥር የሚያካሂዱ የስራ ሂደቶች ያስፈልጉታል። መስከረምና ጥቅምት የእንቦጩ ስርጭት የሚጨምርበት ወቅት እንደመሆኑ ብዙ ስራዎች መሰራት ያለባቸው ከዚህ ወቅት ቀደም ብሎ መሆን ይኖርበታል። አክቲቪስቶችም አመቱን ሙሉ ጣና ትኩረት እንዲሰጠው ቅስቀሳ ቢሰሩ መልካም ነው። ጋዜጠኞች የሚሰራውን ስራ በቅርበት እየተከታተሉ ለህብረተሰቡ ተጨባጭ መረጃ መስጠት አለባቸው። በእኛ በኩል ማህበራችን በአመት ሁለት ጊዜ (በአመቱ አጋማሽና በአመቱ መጨረሻ) የእንቦጩን ስርጭት በተመለከተ የመስክ ግምገማ እያካሄደ ለማቅረብ ጥረት ያደረጋል። ከዚህም በተጨማሪ የሳተላይት መረጃዎችን በማጠናከር የአረሙን ስርጭትና ወቅታዊ እንቅስቃሴ መረጃን ለውሳኔ ሰጭ አካላት እናቀርባለን። በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ ባለሙያዎች የተመሰረተው የጣና ተፋሰስ የተቀናጀ ልማት በጎ አድራጎት ድርጅት ከማህበራችን ጋር በመተባበር በቅርቡ የአረሙን ልኬት ሰርተው ሪፖርት እያዘጋጁ ስለሆነ ሪፖርቱ እንደደረሰን ለህዝብ ይፋ እናደርጋለን።

የዓመቱ የፋይናንስ ሪፖርታችን ከዚህ ጋር ተያይዟል።

CoalitionReport 12 Oct 2018